Friday, February 12, 2010

መጽሐፈ መሣፍንት 1

ምዕራፍ 1።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ኢያሱ ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች። ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን በፊት ይወጣልናል? ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ።

2፤ እግዚአብሔርም። ይሁዳ ይውጣ፤ እነሆ፥ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቻለሁ አለ።

3፤ ይሁዳም ወንድሙን ስምዖንን። ከነዓናውያንን እንወጋ ዘንድ ከእኔ ጋር ወደ ዕጣዬ ውጣ፥ እኔም ደግሞ ከአንተ ጋር ወደ ዕጣህ እሄዳለሁ አለው። ስምዖንም ከእርሱ ጋር ሄደ።

4፤ ይሁዳም ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም በቤዜቅ ውስጥ አሥር ሺህ ሰዎች ገደሉ።

5፤ አዶኒቤዜቅንም በቤዜቅ አገኙትና ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንንም መቱአቸው።

6፤ አዶኒቤዜቅም ሸሸ፤ አሳድደውም ያዙት፥ የእጁንና የእግሩንም አውራ ጣት ቈረጡ።

7፤ አዶኒቤዜቅም። የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣት የተቈረጡ ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ በታች ፍርፋሪ ይለቅሙ ነበር፤ እኔ እንዳደረግሁ እግዚአብሔር እንዲሁ መለሰልኝ አለ። ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፥ በዚያም ሞተ።

8፤ የይሁዳም ልጆች ኢየሩሳሌምን ተዋግተው ያዙአት፥ በሰይፍ ስለትም መቱአት፥ ከተማይቱንም በእሳት አቃጠሉአት።

9፤ ከዚያም በኋላ የይሁዳ ልጆች በተራራማው አገርና በደቡቡ በኩል በቈላውም ውስጥ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጉ ወረዱ።

10፤ ይሁዳም በኬብሮን የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ሊወጋ ሄደ። የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያትአርባቅ ነበረ። ሴሲንና አኪመንን ተላሚንም ገደሉ።

11፤ ከዚያም የዳቤርን ሰዎች ሊወጋ ሄደ፤ አስቀድሞም የዳቤር ስም ቅርያትሤፍር ነበረ።

12፤ ካሌብም። ቅርያትሤፍርን ለሚመታና ለሚይዝ ልጄን ዓክሳን አጋባዋለሁ አለ።

13፤ የካሌብም ትንሽ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ያዛት፤ ልጁንም ዓክሳን አጋባው።

14፤ እርስዋም ወደ እርሱ በመጣች ጊዜ ከአባትዋ እርሻ እንዲለምን መከረችው። እርስዋም ከአህያዋ ወረደች፤ ካሌብም። ምን ፈለግሽ? አላት።

15፤ እርስዋም። በረከትን ስጠኝ፤ በደቡብ በኩል ያለውን ምድር ሰጥተኸኛልና የውኃ ምንጭ ደግሞ ስጠኝ አለችው። ካሌብም ላይኛውንና ታችኛውን ምንጭ ሰጣት።

16፤ የቄናዊው የሙሴ አማት ልጆችም ከይሁዳ ልጆች ጋር ዘንባባ ካለባት ከተማ ተነሥተው ከዓራድ በደቡብ በኩል ወዳለው ወደ ይሁዳ ምድረ በዳ ወጡ፤ ሄደውም ከሕዝቡ ጋር ተቀመጡ።

17፤ ይሁዳም ከወንድሙ ከስምዖን ጋር ሄደ፥ በጽፋት የተቀመጡትንም ከነዓናውያንን መቱ፥ ፈጽመውም አጠፉአት። የከተማይቱንም ስም ሔርማ ብለው ጠሩአት።

18፤ ይሁዳም ጋዛንና ዳርቻዋን፥ አስቀሎናንና ዳርቻዋን፥ አቃሮንንና ዳርቻዋን ያዘ።

19፤ እግዚአብሔርም ከይሁዳ ጋር ነበረ፤ ይሁዳም ተራራማውን አገር ወረሰ፤ በሸለቆው የሚኖሩት ግን የብረት ሰረገሎች ነበሩአቸውና ሊያወጣቸው አልቻለም።

20፤ ሙሴም እንደ ተናገረ ለካሌብ ኬብሮንን ሰጡት፤ ከዚያም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች አወጣ።

21፤ ነገር ግን በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን የብንያም ልጆች አላወጡአቸውም፤ ኢያቡሳውያንም ከብንያም ልጆች ጋር እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል።

22፤ የዮሴፍም ወገን ደግሞ በቤቴል ላይ ወጡ፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ነበረ።

23፤ የዮሴፍም ወገን ቤቴልን የሚሰልሉ ላኩ። አስቀድሞም የከተማይቱ ስም ሎዛ ይባል ነበር።

24፤ ጠባቂዎቹም አንድ ሰው ከከተማ ሲወጣ አይተው። የከተማይቱን መግቢያ አሳየን፥ እኛም ቸርነት እናደርግልሃለን አሉት።

25፤ የከተማይቱንም መግቢያ አሳያቸው፥ ከተማይቱንም በሰይፍ ስለት መቱ፤ ያንን ሰውና ወገኖቹን ግን ለቀቁአቸው።

26፤ ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄደ፥ በዚያም ከተማን ሠራ፥ ስምዋንም ሎዛ ብሎ ጠራት። እስከ ዛሬም ድረስ ስምዋ ይህ ነው።

27፤ ምናሴም የቤትሳንንና የመንደሮችዋን፥ የታዕናክንና የመንደሮችዋን፥ የዶርንና የመንደሮችዋን፥ የይብለዓምንና የመንደሮችዋን፥ የመጊዶንና የመንደሮችዋን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በዚያ አገር በመቀመጥ ጸኑ።

28፤ እስራኤልም በበረቱ ጊዜ ከነዓናውያንን አስገበሩአቸው፥ ፈጽመውም አላወጡአቸውም።

29፤ ኤፍሬምም በጌዝር የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው በጌዝር ተቀመጡ።

30፤ ዛብሎንም የቂድሮንንና የነህሎልን ሰዎች አላወጣቸውም፤ ነገር ግን ከነዓናውያን በመካከላቸው ተቀመጡ፥ ግብርም የሚገብሩለት ሆኑ።

31፤ አሴርም የዓኮንና የሲዶንን የአሕላብንም የአክዚብንም የሒልባንም የአፌቅንም የረአብንም ሰዎች አላወጣቸውም።

32፤ በዚያችም ምድር የተቀመጡትን ከነዓናውያን አላወጡአቸውምና በመካከላቸው የአሴር ልጆች ተቀመጡ።

33፤ ንፍታሌምም የቤትሳሚስንና የቤትዓናትን ሰዎች አላወጣቸውም፥ በምድሩም በተቀመጡት በከነዓናውያን መካከል ተቀመጡ፤ ነገር ግን የቤትሳሚስና የቤትዓናት ሰዎች ግብር የሚገብሩለት ሆኑ።

34፤ አሞራውያንም የዳንን ልጆች ወደ ተራራማው አገር እንዲያፈገፍጉ አስገደዱአቸው፥ ወደ ሸለቆውም እንዳይወርዱ ከለከሉአቸው።

35፤ አሞራውያን በሔሬስ ተራራና በኤሎን በሸዓልቢምም በመቀመጥ ጸኑ፤ ነገር ግን የዮሴፍ ቤት እጅ ከበደች፥ አስገበረቻቸውም።

36፤ የአሞራውያንም ድንበር ከአቅረቢም ዐቀበት ከጭንጫው ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ነበረ።

መጽሐፈ መሣፍንት 2

ምዕራፍ 2።

1፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ከጌልገላ ወደ ቦኪም ወጥቶ እንዲህ አለ። እኔ ከግብፅ አውጥቻችኋለሁ፥ ለአባቶቻችሁም ወደ ማልሁላቸው ምድር አግብቻችኋለሁ፤ እኔም። ከእናንተ ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ለዘላለም አላፈርስም፤

2፤ እናንተም መሠዊያቸውን አፍርሱ እንጂ በዚህች ምድር ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን አታድርጉ አልሁ። እናንተ ግን ቃሌን አልሰማችሁም፤

3፤ ይህንስ ለምን አደረጋችሁ? ስለዚህም። ከፊታችሁ አላወጣቸውም፥ ነገር ግን ያስጨንቋችኋል፥ አማልክቶቻቸውም ወጥመድ ይሆኑባችኋል አልሁ።

4፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ይህን ቃል ለእስራኤል ልጆች ሁሉ በተናገረ ጊዜ ሕዝቡ ድምፃቸውን አንሥተው አለቀሱ።

5፤ የዚያንም ስፍራ ስም ቦኪም ብለው ጠሩት፤ በዚያም ለእግዚአብሔር ሠዉ።

6፤ ኢያሱም ሕዝቡን ባሰናበተ ጊዜ የእስራኤል ልጆች ምድሪቱን ሊወርሱ ወደ እየርስታቸው ሄዱ።

7፤ ኢያሱም በነበረበት ዘመን ሁሉ፥ ለእስራኤልም ያደረገውን ታላቁን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ ባዩት፥ ከኢያሱ በኋላ በነበሩ ሽማግሌዎች ዘመን ሁሉ፥ ሕዝቡ እግዚአብሔርን አመለኩ።

8፤ የእግዚአብሔርም ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ አሥር ዓመት ሲሆነው ሞተ።

9፤ በተራራማውም በኤፍሬም አገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሔሬስ ቀበሩት።

10፤ ትውልድ ሁሉ ደግሞ ወደ አባቶቻቸው ተከማቹ፤ ከእነዚያም በኋላ እግዚአብሔርን ለእስራኤልም ያደረገውን ሥራ ያላወቀ ሌላ ትውልድ ተነሣ።

11፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ፥ በኣሊምንም አመለኩ።

12፤ ከግብፅ ምድርም ያወጣቸውን የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ተዉ፥ በዙሪያቸውም ካሉት ከአሕዛብ አማልክት ሌሎችን አማልክት ተከተሉ፥ ሰገዱላቸውም፤ እግዚአብሔርንም አስቈጡ።

13፤ እግዚአብሔርንም ትተው በኣልንና አስታሮትን አመለኩ።

14፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ወደ ማረኩአቸውም ማራኪዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ በዙሪያቸውም ባሉት በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ጠላቶቻቸውንም ከዚያ ወዲያ ሊቋቋሙ አልቻሉም።

15፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ፥ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ እንደማለ፥ ወደ ወጡበት ሁሉ የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበረች፤ እጅግም ተጨነቁ።

16፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን አስነሣላቸው፥ ከሚማርኩአቸውም እጅ አዳኑአቸው።

17፤ ሌሎች አማልክትን ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም እንጂ መሳፍንቶቻቸውን አልሰሙም፤ አባቶቻቸውም ይሄዱበት ከነበረ መንገድ ፈጥነው ፈቀቅ አሉ፤ አባቶቻቸው ለእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደ ታዘዙ እንዲሁ አላደረጉም።

18፤ እግዚአብሔርም መሳፍንትን ባስነሣላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ከመስፍኑ ጋር ነበረ፤ እግዚአብሔርም ስለሚጋፉአቸውና ስለሚያስጨንቋቸው በጩኸታቸው ያዝን ነበርና በመስፍኑ ዘመን ሁሉ ከጠላቶቻቸው እጅ አዳናቸው።

19፤ መስፍኑ ግን ከሞተ በኋላ ይመለሱ ነበር፥ ሌሎችንም አማልክት በመከተላቸው እነርሱንም በማምለካቸውና ለእነርሱ በመስገዳቸው አባቶቻቸው አድርገውት ከነበረው የከፋ ያደርጉ ነበር፤ የእልከኝነታቸውን መንገድና ሥራቸውን አልተዉም ነበር።

20፤ የእግዚአብሔርም ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ እንዲህም አለ። ይህ ሕዝብ ለአባቶቻቸው ያዘዝሁትን ቃል ኪዳን ስለ ተላለፉ፥ ድምፄንም ስላልሰሙ አባቶቻቸውም እንደ ጠበቁ፥

21፤22፤ ይሄዱባት ዘንድ የእግዚአብሔርን መንገድ ይጠብቁ ወይም አይጠብቁ እንደ ሆነ እስራኤልን እፈትንባቸው ዘንድ፥ ኢያሱ በሞተ ጊዜ ከተዋቸው አሕዛብ አንዱን ሰው እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ ከፊታቸው አላወጣም።

23፤ እግዚአብሔርም እነዚህን አሕዛብ አስቀረ፥ ፈጥኖም አላወጣቸውም፥ በኢያሱም እጅ አሳልፎ አልሰጣቸውም።

መጽሐፈ መሣፍንት 3

ምዕራፍ 3።

1፤2፤ ከከነዓናውያንም ጋር መዋጋት ያላወቁትን እስራኤልን በእነርሱ ይፈትናቸው ዘንድ፥ በፊትም ሰልፍን ያልለመዱ የእስራኤል ልጆች ትውልድ መዋጋትን ያውቁና ይማሩ ዘንድ እግዚአብሔር ያስቀራቸው አሕዛብ እነዚህ ናቸው፤

3፤ አምስቱ የፍልስጥኤማውያን መኳንንት፥ ከነዓናውያንም ሁሉ፥ ሲዶናውያንም፥ ከበኣልአርሞንዔም ተራራ ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ ድረስ በሊባኖስ ተራራ የሚኖሩትም ኤዊያውያን።

4፤ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ለአባቶቻቸው ያዘዘውን ትእዛዝ መስማታቸው እንዲታወቅ እስራኤል ይፈተኑባቸው ዘንድ እነዚህ ቀሩ።

5፤ የእስራኤልም ልጆች በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ።

6፤ ሴት ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።

7፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነውን ነገር አደረጉ፥ አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረስተው በኣሊምንና አስታሮትን አመለኩ።

8፤ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የእስራኤልም ልጆች ለኵሰርሰቴም ስምንት ዓመት ተገዙለት።

9፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው።

10፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእርሱ ላይ መጣ፥ በእስራኤልም ላይ ይፈርድ ነበር፤ ለሰልፍ ወጣ፥ እግዚአብሔርም የመስጴጦምያን ንጉሥ ኵሰርሰቴምን በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እጁም በኵሰርሰቴም ላይ አሸነፈች።

11፤ ምድሪቱም አርባ ዓመት ዐረፈች፤ የቄኔዝም ልጅ ጎቶንያል ሞተ።

12፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ስለ ሠሩ እግዚአብሔር የሞዓብን ንጉሥ ዔግሎምን በእስራኤል ላይ አበረታባቸው።

13፤ የአሞንን ልጆችና አማሌቅን ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ ሄዶም እስራኤልን መታ፥ ዘንባባም ያለባትን ከተማ ያዙአት።

14፤ የእስራኤልም ልጆች ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎም አሥራ ስምንት ዓመት ተገዙለት።

15፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ።

16፤ ናዖድም ሁለት አፍ ያለው ርዝመቱ አንድ ክንድ የሆነ ሰይፍ አበጀ፥ ከልብሱም በታች በቀኝ ጭኑ በኩል አደረገው።

17፤ ለሞዓብም ንጉሥ ለዔግሎም ግብሩን አቀረበ፤ ዔግሎምም እጅግ ወፍራም ሰው ነበረ።

18፤ ግብሩንም ማቅረብ በጨረሰ ጊዜ፥ ግብር የተሸከሙትን ሰዎች ሰደደ።

19፤ ናዖድ ግን በጌልገላ ከነበሩት ትክል ድንጋዮች ዘንድ ተመልሶ። ንጉሥ ሆይ፥ የምሥጢር ነገር አለኝ አለ፤ ንጉሡም። ዝም በል አለ፤ በዙሪያውም የቆሙት ሁሉ ወጡ።

20፤ ናዖድም ወደ እርሱ ቀረበ፤ እርሱም በሰገነት ቤት ለብቻው ተቀምጦ ነበር። ናዖድም። የእግዚአብሔር መልእክት ለአንተ አለኝ አለ። ከዙፋኑም ተነሣ።

21፤ ናዖድም ግራ እጁን ዘርግቶ ከቀኝ ጭኑ ሰይፉን ወሰደ፥ ሆዱንም ወጋው፤

22፤ የሰይፉም እጀታው ደግሞ ከስለቱ በኋላ ገባ፤ ስቡም ስለቱን ከደነው፥ ሰይፉንም ከሆዱ መልሶ አላወጣውም፤ በኋላውም ወጣ።

23፤ ናዖድም ወደ ደርቡ ወጣ፥ የሰገነቱንም ደጅ ዘግቶ ቈለፈው።

24፤ ናዖድም ከሄደ በኋላ ባሪያዎቹ መጡ፤ የሰገነቱም ደጅ ተቈልፎ ባዩ ጊዜ። ምናልባት በሰገነቱ ውስጥ ወገቡን ይሞክር ይሆናል አሉ።

25፤ እስኪያፍሩም ድረስ እጅግ ዘገዩ፤ የሰገነቱንም ደጅ እንዳልከፈተ ባዩ ጊዜ መክፈቻውን ወስደው ከፈቱ፥ እነሆም፥ ጌታቸው በምድር ወድቆ ሞቶም አገኙት።

26፤ በዘገዩበትም ጊዜያት ናዖድ ሸሸ፥ ትክል ድንጋዮቹንም አለፈ፥ ወደ ቤይሮታም አመለጠ።

27፤ በመጣም ጊዜ በተራራማው በኤፍሬም አገር ቀንደ መለከት ነፋ፤ የእስራኤልም ልጆች ከእርሱ ጋር ከተራራማው አገር ወረዱ፥ እርሱም በፊታቸው ሄደ።

28፤ እርሱም። እግዚአብሔር ጠላቶቻችሁን ሞዓባውያንን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአልና ተከተሉኝ አላቸው። ተከትለውትም ወረዱ፥ ወደ ሞዓብም የሚያሻግረውን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙ፥ ማንንም አላሳለፉም።

29፤ የዚያን ጊዜም ከሞዓብ አሥር ሺህ የሚያህሉትን፥ ጕልማሶችና ጽኑዓን ሁሉ፥ መቱ፤ አንድ እንኳ አላመለጠም።

30፤ በዚያም ቀን ሞዓብ ከእስራኤል እጅ በታች ተዋረደ፤ ምድሪቱም ሰማንያ ዓመት ዐረፈች።

31፤ ከእርሱም በኋላ የዓናት ልጅ ሰሜጋር ተነሣ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ስድስት መቶ ሰው በበሬ መውጊያ ገደለ፤ እርሱም ደግሞ እስራኤልን አዳነ።

መጽሐፈ መሣፍንት 4

ምዕራፍ 4።

1፤ ናዖድም ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት እንደ ገና ክፉ ሥራ ሠሩ።

2፤ እግዚአብሔርም በአሶር በነገሠው በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ የሠራዊቱም አለቃ በአሕዛብ አሪሶት የተቀመጠው ሲሣራ ነበረ።

3፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች ነበሩትና፥ የእስራኤልንም ልጆች ሀያ ዓመት ያህል እጅግ ያስጨንቃቸው ነበር።

4፤ በዚያ ጊዜም ነቢይቱ የለፊዶት ሚስት ዲቦራ በእስራኤል ላይ ትፈርድ ነበረች።

5፤ እርስዋም በተራራማው በኤፍሬም አገር በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዛፍ ከሚባለው ከዘንባባው በታች ተቀምጣ ነበር፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እርስዋ ለፍርድ ይወጡ ነበር።

6፤ ልካም ከቃዴስ ንፍታሌም የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅን ጠርታ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። ሄደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፥ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አሥር ሺህ ሰዎች ውሰድ፤

7፤ እኔም የኢያቢስን ሠራዊት አለቃ ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሕዝቡንም ሁሉ ወደ አንተ ወደ ቂሶን ወንዝ እስባለሁ፥ በእጅህም አሳልፌ እሰጠዋለሁ ብሎ አላዘዘህምን? አለችው።

8፤ ባርቅም። አንቺ ከእኔ ጋር ብትሄጂ እኔ እሄዳለሁ፤ አንቺ ግን ከእኔ ጋር ባትሄጂ እኔ አልሄድም አላት።

9፤ እርሷም። በእውነት ከአንተ ጋር እሄዳለሁ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሲሣራን በሴት እጅ አሳልፎ ይሰጣልና በዚህ በምትሄድበት መንገድ ለአንተ ክብር አይሆንም አለችው። ዲቦራም ተነሥታ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች።

10፤ ባርቅም ዛብሎንንና ንፍታሌምን ወደ ቃዴስ ጠራቸው፥ አሥር ሺህም ሰዎች ተከትለውት ወጡ፤ ዲቦራም ከእርሱ ጋር ወጣች።

11፤ ቄናዊውም ሔቤር ከሙሴ አማት ከኦባብ ልጆች ከቄናውያን ተለይቶ ድንኳኑን በቃዴስ አጠገብ በጻዕናይም እስከ ነበረው እስከ ትልቁ ዛፍ ድረስ ተከለ።

12፤ የአቢኒኤምም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ እንደ ወጣ ለሲሣራ ነገሩት።

13፤ ሲሣራም ሰረገሎቹን ሁሉ፥ ዘጠኝ መቶ የብረት ሰረገሎች፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን ሕዝቡን ሁሉ ከአሪሶት ወደ ቂሶን ወንዝ ሰበሰባቸው።

14፤ ዲቦራም ባርቅን። እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባርቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ።

15፤ እግዚአብሔርም ሲሣራን ሰረገሎቹንም ሁሉ ሠራዊቱንም ሁሉ ከባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት አስደነገጣቸው፤ ሲሣራም ከሰረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ።

16፤ ባርቅም ሰረገሎችንና ሠራዊቱን እስከ አሪሶት ድረስ አባረረ፤ የሲሣራም ሠራዊት ሁሉ በሰይፍ ስለት ወደቀ፤ አንድ እንኳ አልቀረም።

17፤ በአሶር ንጉሥም በኢያቢስና በቄናዊው በሔቤር ቤት መካከል ሰላም ነበረና ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ ወደ ቄናዊው ወደ ሔቤር ሚስት ወደ ኢያዔል ድንኳን ደረሰ።

18፤ ኢያዔልም ሲሣራን ለመገናኘት ወጥታ። ግባ፥ ጌታዬ ሆይ፥ ወደ እኔ ግባ፤ አትፍራ አለችው። ወደ እርስዋም ወደ ድንኳንዋ ገባ፥ በመጐናጸፊያዋም ሸፈነችው።

19፤ እርሱም። ጠምቶኛልና እባክሽ የምጠጣው ጥቂት ውኃ ስጭኝ አላት፤ እርስዋም የወተቱን አቁማዳ ፈትታ አጠጣችው፥ ሸፈነችውም።

20፤ እርሱም። ከድንኳኑ ደጃፍ ቁሚ፤ ሰውም መጥቶ። በዚህ ሰው አለን? ብሎ ቢጠይቅሽ አንቺ። የለም ትዪዋለሽ አላት።

21፤ የሔቤርም ሚስት ኢያዔል የድንኳን ካስማ ወሰደች፥ በእጅዋም መዶሻ ያዘች፥ ቀስ ብላም ወደ እርሱ ቀረበች፤ በጆሮግንዱ ካስማውን ቸነከረች፤ እርሱም ደክሞ እንቀላፍቶ ነበርና ካስማው ወደ መሬት ጠለቀ፥ እርሱም ሞተ።

22፤ እነሆም፥ ባርቅ ሲሣራን ሲያባርር ኢያዔል ልትገናኘው ወጥታ። ና የምትሻውንም ሰው አሳይሃለሁ አለችው። ወደ እርስዋም ገባ፥ እነሆም፥ ሲሣራን ወድቆ ሞቶም አገኘው፥ ካስማውም ከጆሮግንዱ ውስጥ ነበረ።

v23፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤል ልጆች ፊት አዋረደ።

24፤ የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስንም እስኪያጠፉ ድረስ በከነዓን ንጉሥ በኢያቢስ ላይ የእስራኤል ልጆች እጅ እየበረታች ሄደች።

መጽሐፈ መሣፍንት 5

መጽሐፈ መሣፍንት 5

ምዕራፍ 5።

1፤ በዚያም ቀን ዲቦራና የአቢኒኤም ልጅ ባርቅ እንዲህ ብለው ተቀኙ።

2፤ በእስራኤል ውስጥ መሪዎች ስለ መሩ፥

ሕዝቡም ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ስለ ሰጡ፥

እግዚአብሔርን አመስግኑ።


3፤ ነገሥታት ሆይ፥ ስሙ፤

መኳንንት ሆይ፥ አድምጡ፤

እኔ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፥

ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።

4፤ አቤቱ፥ ከሴይር በወጣህ ጊዜ፥

ከኤዶምያስም ሜዳ በተራመድህ ጊዜ፥

ምድሪቱ ተናወጠች፥ ሰማያቱም አንጠበጠቡ፤

ደመናትም ደግሞ ውኃን አንጠበጠቡ።

5፤ ተራሮች ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ ቀለጡ፥

ያም ሲና ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ፊት የተነሣ።

6፤ በዓናት ልጅ በሰሜጋር ዘመን፥

በኢያዔል ዘመን መንገዶች ተቋረጡ፤

መንገደኞች በስርጥ መንገድ ይሄዱ ነበር።

7፤ አንቺ፥ ዲቦራ፥ እስክትነሽ ድረስ፥

ለእስራኤልም እናት ሆነሽ እስክትነሽ ድረስ፥

ኃያላን በእስራኤል ዘንድ አነሱ፥ አለቁም።

8፤ አዲሶች አማልክትን መረጡ፤

በዚያ ጊዜ ሰልፍ በበሮች ሆነ፤

በአርባ ሺህ በእስራኤል ዘንድ ጦርና ጋሻ አልታየም።

9፤ ልቤ ወደ እስራኤል አለቆች ነው፥

በሕዝቡ መካከል ነፍሳቸውን በፈቃዳቸው ወደ ሰጡት፤

እግዚአብሔርን አመስግኑ።

10፤ በነጫጭ አህዮች ላይ የምትጫኑ፥

በወላንሳ ላይ የምትቀመጡ፥

በመንገድም የምትሄዱ፥ ተናገሩ።

11፤ በማጠጫው መካከል ካሉት ከቀስተኞች ጩኸት ርቀው፥

በዚያ የእግዚአብሔርን ጽድቅ፥

በእስራኤል ላይ የግዛቱን ጽድቅ ይጫወታሉ፤

ከዚያም በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ ወደ በሮች ወረዱ።

12፤ ንቂ፥ ንቂ፥ ዲቦራ ሆይ፤

ንቂ፥ ንቂ፥ ቅኔውን ተቀኚ፤

ባርቅ ሆይ፥ ተነሣ፤

የአቢኒኤም ልጅ ሆይ፥ ምርኮህን ማርክ።

13፤ በዚያ ጊዜ የቀሩት ወደ ኃያላኑና ወደ ሕዝቡ ወረዱ፤

እግዚአብሔርም ስለ እኔ በኃያላን ላይ ወረደ።

14፤ በአማሌቅ ዘንድ ሥር የነበራቸው እነርሱ ከኤፍሬም፥

ብንያም ሆይ፥ በሕዝብህ መካከል ከአንተ በኋላ ወረዱ፤

አለቆች ከማኪር፥ የንጉሥንም ዘንግ የሚይዙ ከዛብሎን ወረዱ።

15፤ የይሳኮርም አለቆች ከዲቦራ ጋር ነበሩ፤

ይሳኮርም እንደ ባርቅ ነበረ፤

ከእግሩ በኋላ ወደ ሸለቆው ቸኰሉ፤

በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ብዙ የልብ ማመንታት ነበረ።

16፤ መንጎች ሲያፍዋጩ ለመስማት

በበጎች ጕረኖ መካከል ለምን ተቀመጥህ?

በሮቤል ፈሳሾች አጠገብ ታላቅ የልብ ምርምር ነበረ።

17፤ ገለዓድ በዮርዳኖስ ማዶ ተቀመጠ፤

ዳንም ለምን በመርከብ ውስጥ ቀረ?

አሴርም በባሕሩ ዳር ተቀመጠ፥

በወንዞቹም ዳርቻ ዐረፈ።

18፤ ዛብሎን ነፍሱን ወደ ሞት ያሳለፈ ሕዝብ ነው፥

ንፍታሌምም በአገሩ ኮረብታ ላይ ነው።

19፤ ነገሥታት መጡ፥ ተዋጉም፤

በዚያ ጊዜ በመጊዶ ውኆች አጠገብ በታዕናክ

የከነዓን ነገሥታት ተዋጉ፤

የብር ዘረፋም አልወሰዱም።

20፤ ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤

በአካሄዳቸውም ከሲሣራ ጋር ተዋጉ።

21፤ ከዱሮ ጀምሮ የታወቀ ያ የቂሶን ወንዝ፥

የቂሶን ወንዝ ጠርጎ ወሰዳቸው።

ነፍሴ ሆይ፥ በኃይል እርገጪ።

22፤ ከኃያላን ግልቢያ ብርታት የተነሣ

የፈረሶች ጥፍሮች ተቀጠቀጡ።

23፤ የእግዚአብሔር መልአክ። ሜሮዝን እርገሙ፤

እግዚአብሔርን በኃያላን መካከል ለመርዳት፥

እግዚአብሔርን ለመርዳት አልመጡምና

የተቀመጡባትን ሰዎች ፈጽማችሁ እርገሙ አለ።

24፤ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ኢያዔል

ከሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን፤

በድንኳን ውስጥ ከሚኖሩ ሴቶች ይልቅ የተባረከች ትሁን።

25፤ ውኃ ለመነ፥ ወተትም ሰጠችው፤

በተከበረ ዳካ እርጎ አቀረበችለት።

26፤ እጅዋን ወደ ካስማ፥

ቀኝ እጅዋንም ወደ ሠራተኛ መዶሻ አደረገች፤

በመዶሻውም ሲሣራን መታች፥ ራሱንም ቸነከረች፤

ጆሮግንዱንም በሳች፥ ጎዳችውም።

27፤ በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፥ ተኛ፤

በእግሮችዋ አጠገብ ተደፋ፥ ወደቀ፤

በተደፋበት ስፍራ በዚያ ወድቆ ሞተ።

28፤ ከመስኮት ሆና ተመለከተች፤

የሲሣራ እናት በሰቅሰቅ ዘልቃ።

ስለ ምን ለመምጣት ሰረገላው ዘገየ?

ስለ ምንስ የሰረገላው መንኰራኵር ቈየ? ብላ ጮኸች።

29፤ ብልሃተኞች ሴቶችዋ መለሱላት፤

እርስዋ ደግሞ ለራስዋ እንዲህ ብላ መለሰች።

30፤ ምርኮ አግኝተው የለምን? ተካፍለውስ የለምን?

ለእያንዳንዱ ሰው ምርኮ አንዲት ወይም ሁለት ቈነጃጅት፤

ለሲሣራ ምርኮ ልዩ ልዩ ያለው ልብስ፥

በአንገትጌ ላይ በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጕርጕር ልብስ።

31፤ አቤቱ፥ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤

ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፥ እንዲሁ ይሁኑ። ምድሪቱም አርባ ዓመት ያህል ዐረፈች።

መጽሐፈ መሣፍንት 6

ምዕራፍ 6።

1፤ የእስራኤልም ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ሥራ ሠሩ፤ እግዚአብሔርም በምድያም እጅ ሰባት ዓመት አሳልፎ ሰጣቸው።

2፤ የምድያምም እጅ በእስራኤል ላይ ጠነከረች፤ ከምድያምም የተነሣ የእስራኤል ልጆች በተራራ ላይ ጕድጓድና ዋሻ ምሽግም አበጁ።

3፤ እስራኤልም ዘር በዘሩ ጊዜ ምድያማውያን አማሌቃውያንም በምሥራቅም የሚኖሩ ሰዎች ይመጡባቸው ነበር፤

4፤ በእነርሱም ላይ ይሰፍሩ ነበር፥ እስከ ጋዛም ድረስ የምድሩን ቡቃያ ያጠፉ ነበር፥ ምግብንም ለእስራኤል አይተዉም ነበር፤ በግ ወይም በሬ ወይም አህያ ቢሆን አይተዉም።

5፤ እንስሶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው በብዛት እንደ አንበጣ ሆነው ይመጡ ነበር፤ ለእነርሱና ለግመሎቻቸውም ቍጥር አልነበራቸውም፤ ምድሪቱንም ያጠፉ ዘንድ ይመጡ ነበር።

6፤ ከምድያምም የተነሣ እስራኤል እጅግ ተጠቁ፤ የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

7፤ እንዲህም ሆነ፤ የእስራኤል ልጆች በምድያም ምክንያት ወደ እግዚአብሔር በጮኹ ጊዜ፥

8፤ እግዚአብሔር ወደ እስራኤል ልጆች ነቢይ ላከ፥ እርሱም አለ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፥ ከባርነትም ቤት አስለቀቅኋችሁ፤

9፤ ከግብፃውያንም እጅ፥ ከሚጋፉአችሁም ሁሉ እጅ አዳንኋችሁ፥ ከፊታችሁም አሳደድኋቸው፥ አገራቸውንም ሰጠኋችሁ፤

10፤ እናንተንም። እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ፤ በምድራቸው የተቀመጣችሁባቸውን የአሞራያውያንን አማልክት አትፍሩ አልኋችሁ። እናንተ ግን ድምፄን አልሰማችሁም።

11፤ የእግዚአብሔርም መልአክ መጥቶ በዖፍራ ባለችው ለአቢዔዝራዊው ለኢዮአስ በነበረችው በአድባሩ ዛፍ በታች ተቀመጠ፤ ልጁም ጌዴዎን ከምድያማውያን ለመሸሸግ በወይን መጥመቂያው ውስጥ ስንዴ ይወቃ ነበር።

12፤ የእግዚአብሔርም መልአክ ለእርሱ ተገልጦ። አንተ ጽኑዕ ኃያል ሰው፥ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው አለው።

13፤ ጌዴዎንም። ጌታዬ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ነገር ሁሉ ለምን ደረሰብን? አባቶቻችንስ። እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶናል ብለው ይነግሩን የነበረ ተአምራቱ ወዴት አለ? ወዴት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፥ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል አለው።

14፤ እግዚአብሔርም ወደ እርሱ ዘወር ብሎ። በዚህ በጕልበትህ ሂድ፥ እስራኤልንም ከምድያም እጅ አድን፤ እነሆ፥ ልኬሃለሁ አለው።

15፤ እርሱም። ጌታ ሆይ፥ እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ ከምናሴ ነገድ ከሁሉ ይልቅ የተጠቃ ነው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ አለው።

16፤ እግዚአብሔርም። በእርግጥ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ ምድያምንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታለህ አለው።

17፤ እርሱም። በአንተ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ፥ የምትናገረኝም አንተ እንደ ሆንህ ምልክት አሳየኝ፤

18፤ ወደ አንተም እስክመለስ ድረስ፥ ቍርባኔንም አምጥቼ እስካቀርብልህ ድረስ፥ እባክህ፥ ከዚህ አትላወስ አለው። እርሱም። እስክትመለስ ድረስ እቆያለሁ አለ።

19፤ ጌዴዎን ገባ የፍየሉንም ጠቦት የኢፍ መስፈሪያም ዱቄት የቂጣ እንጎቻ አዘጋጀ፤ ሥጋውን በሌማት አኖረ፥ መረቁንም በምንቸት ውስጥ አደረገ፥ ሁሉንም ይዞ በአድባሩ ዛፍ በታች አቀረበለት።

20፤ የእግዚአብሔርም መልአክ። ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ ወስደህ በዚህ ድንጋይ ላይ አኑር፥ መረቁንም አፍስስ አለው። እንዲሁም አደረገ።

21፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በእጁ ያለውን የበትሩን ጫፍ ዘርግቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ አስነካ፤ እሳትም ከድንጋዩ ውስጥ ወጥቶ ሥጋውንና የቂጣውን እንጎቻ በላ። የእግዚአብሔርም መልአክ ከዓይኑ ተሰወረ።

22፤ ጌዴዎንም የእግዚአብሔር መልአክ እንደ ሆነ አየ፤ ጌዴዎንም። አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና አለ።

23፤ እግዚአብሔርም። ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም አለው።

24፤ ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ ስሙንም። እግዚአብሔር ሰላም ብሎ ጠራው። እርሱም እስከ ዛሬ ድረስ ለአቢዔዝራውያን በምትሆነው በዖፍራ አለ።

25፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት። የአባትህን በሬ፥ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን በሬ፥ ውሰድ፥ የአባትህ የሆነውንም የበኣል መሠዊያ አፍርስ፥ በእርሱም ዙሪያ ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቍረጥ፤

26፤ በዚያም ኮረብታ አናት ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ አሳምረህ ሥራ ሁለተኛውንም በሬ ውሰድ፥ በዚያም በቈረጥኸው በማምለኪያ ዐፀዱ እንጨት ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ አለው።

27፤ ጌዴዎንም ከባሪያዎቹ አሥር ሰዎችን ወስዶ እግዚአብሔር እንዳለው አደረገ፤ የአባቱን ቤተ ሰቦች የከተማውንም ሰዎች ስለ ፈራ ይህን በቀን ለማድረግ አልቻለም፥ ነገር ግን በሌሊት አደረገው።

28፤ የከተማውም ሰዎች ማልደው ተነሡ፥ እነሆም፥ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ፥ በዙሪያው ያለውም የማምለኪያ ዐፀድ ተቈርጦ፥ በተሠራውም መሠዊያ ላይ ሁለተኛው በሬ ተሠውቶ አገኙት።

29፤ እርስ በርሳቸውም። ይህን ነገር ያደረገ ማን ነው? ተባባሉ። በጠየቁና በመረመሩም ጊዜ። ይህን ነገር ያደረገ የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን ነው አሉ።

30፤ የከተማውም ሰዎች ኢዮአስን። የበኣልን መሠዊያ አፍርሶአልና፥ በዙሪያውም ያለውን የማምለኪያ ዐፀድ ቈርጦአልና እንዲሞት ልጅህን አውጣ አሉት።

31፤ ኢዮአስም እርሱን የተቃወሙትን ሁሉ። ለበኣል ትምዋገቱለታላችሁን? ወይስ እርሱን ታድናላችሁን? የሚምዋገትለት ሁሉ እስከ ነገ ይሙት፤ እርሱ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ካፈረሰው ጋር ለራሱ ይምዋገት አላቸው።

32፤ ስለዚህም በዚያ ቀን። መሠዊያውን አፍርሶአልና በኣል ከእርሱ ጋር ይምዋገት ብሎ ጌዴዎንን። ይሩበኣል ብሎ ጠራው።

33፤ ምድያማውያንም አማሌቃውያንም ሁሉ የምሥራቅም ሰዎች አንድ ሆነው ተሰበሰቡ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በኢይዝራኤልም ሸለቆ ሰፈሩ።

34፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በጌዴዎን ገባበት፥ እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ የአቢዔዝርም ሰዎች ተጠርተው በኋላው ተከተሉት።

35፤ ወደ ምናሴም ነገድ ሁሉ መልክተኞችን ሰደደ እነርሱም ደግሞ ተጠርተው በኋላው ተከተሉት፤ መልክተኞችንም ወደ አሴርና ወደ ዛብሎን ወደ ንፍታሌምም ሰደደ፥ እነርሱም ሊገናኙአቸው ወጡ።

36፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ ታድን እንደ ሆነ፥

37፤ እነሆ፥ በአውድማው ላይ የተባዘተ የበግ ጠጕር አኖራለሁ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ጠል ቢሆን በምድሩም ሁሉ ደረቅ ቢሆን፥ እንደ ተናገርህ የእስራኤልን ልጆች በእኔ እጅ እንድታድናቸው አውቃለሁ አለ።

38፤ እንዲሁም ሆነ፤ በነጋውም ማልዶ ተነሣ፥ ጠጕሩንም ጨመቀው፥ ከጠጕሩም የተጨመቀው ጠል ቆሬ ሙሉ ውኃ ሆነ።

39፤ ጌዴዎንም እግዚአብሔርን። እኔ ይህን አንድ ጊዜ ስናገር አትቈጣኝ፤ እኔ ይህን አንድ ጊዜ በጠጕሩ፥ እባክህ፥ ልፈትን፤ አሁንም በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ይሁን፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ይሁን አለው።

40፤ እግዚአብሔርም በዚያ ሌሊት እንዲሁ አደረገ፤ በጠጕሩ ብቻ ላይ ደረቅ ነበረ፥ በምድሩም ሁሉ ላይ ጠል ነበረ። a